የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከጃፓን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጋር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከጃፓን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጋር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዶዳይ ከተሰኘ የጃፓን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጋር በትራንስፖርት ዘርፍ በጋራ መስራት ሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታየ(ዶ/ር) እና የዶዳይ ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ዩማ ሳሳኪ ፈርመዋል፡፡
ዶክተር ብሩክ ታየ በዚሁ ወቅት፤ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂና አመች የትራንስፖርት አገልግሎት ለመዘርጋት ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ትብብሩ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ሞተር ብስክሌቶችን በስፋት በማቅረብ የትራንስፖርት ስርዓቱን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይል ላይ የተመሰረተ የትራንስፖርት ስርዓት በመዘርጋት የካርበን ልቀትን በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስምምነቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የዶዳይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ዩማ ሳሳኪ በበኩላቸው፤ ይህ አጋርነት የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ዘርፍ የለውጥ ሂደት የሚደግፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኩባንያው በ12 ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ ብቻ 100 የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎችን የመክፈት እቅድ እንዳለው ገልጸዋል።
በሦስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ የአዲስ አበባ እና የሸገር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌት ፍላጎትን የማዳረስ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡