ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሳተፉበት የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ የተሳተፉበት የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል።

በውድድሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የቀድሞ ኮከብ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋቾች ተሳትፈዋል።

ከቀድሞ ኮከብ የአፍሪካ አገራት ተጫዋቾች መካከልም ሳሙኤል ኤቶ፣ ኦኮቻ፣ ከሀገር ውስጥ ሳላዲን ደግሞ ሰኢድ፣ አዳነ ግርማን ጨምሮ የካፍ አመራሮች እና የሌሎች አፍሪካ አገራት ኮከብ ተጫዋቾች ይገኙበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመላው አገሪቱ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲገነቡ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ማስገንባታቸውም እንዲሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ ዛሬ ጠዋት በግንባታ ላይ የሚገኘውን የአደይ አበባ ስታዲየምን መጎብኘታቸው ይታወቃል።


 

ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝም የናይጄሪያ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዳንኤል አሞካቺና ንዋንኩ ካኑ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተመርጠው ጥረቶች መጀመራቸው መጥቀሳቸውም እንዲሁ።

46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጠቅላላ ጉባዔ ነገ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም