የኢትዮ-ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
በነገው እለት በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የኢትዮጵያና የኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም በማስመልከት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፤ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በፎረሙ የሁለቱ አገራት ግዙፍ ኩባንያዎች የሚሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ አጋጣሚው የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑንም ገልፀዋል።
የኦስትሪያ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማየት የሚመጡ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ናፕ (ዶ/ር)፤ በቢዝነስ ፎረሙ በጤና እንዲሁም በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች የሚሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
የፎረሙ መካሄድ የጋራ ልምድን ከመቀመርና ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
የቢዝነስ ፎረሙ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑ ታውቋል።