የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ ሎጅስቲክስ አገልግሎቱን ከ10 በመቶ በላይ ለማሳደግ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ ሎጅስቲክስ አገልግሎቱን ከ10 በመቶ በላይ ለማሳደግ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 በጀት ዓመት የካርጎ ሎጅስቲክስ አገልግሎትን ከ10 በመቶ በላይ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ የአየር መንገዱን የካርጎ ሎጅስቲክስ አገልግሎትን በተመለከተ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የካርጎ ጭነት አገልግሎት የሚሰጡ 16 ግዙፍና መካከለኛ አውሮፕላኖች እንዳሉት ጠቅሰው በቀጣይም በተቀላጠፈና ሰፊ መዳረሻ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በ140 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የተለያዩ የጭነት አገልግሎቶችን እያጓጓዘ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ከ758 ሺህ ቶን በላይ ጭነት ተጓጉዞ ከአጠቃላይ ገቢው የካርጎ ዘርፍ 1 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመትም አየር መንገዱ የካርጎ ሎጅስቲክስ ዘርፉን ከ10 በመቶ በላይ ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጭነት ትራንስፖርት ደረቅና ቶሎ የሚበላሹ ምርቶችን እንዲሁም ልዩ አያያዝ የሚፈልጉትን በመለየት በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አብራርተዋል።
በ2016 በጀት አመት በ50 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባው ዘመናዊ የኢ-ኮሜርስ የጭነት አገልግሎት ማዕከል ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በመፈራረም ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተው በቀጣይም የኢ-ኮሜርስ አገልግሎቱን እያሰፋ እንደሚሄድ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ2016 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 02 ቢሊየን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱ ይታወሳል።
አየር መንገዱ እኤአ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን 25 ቢሊየን ዶላር ለማድረስና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።