ቀጥታ፡

በክላስተር ከለማው ስንዴ የተሻለ ምርት ለማግኘት ለሰብል እንክብካቤ ሥራ ትኩረት ሰጥተናል

ሀዋሳ ፤ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦ በመኸር እርሻ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎችን በመጠቀም በክላስተር ካለሙት የስንዴ ሰብል የተሻለ ምርት ለማግኘት ለሰብል እንክብካቤ ሥራ ትኩረት መስጠታቸውን በሲዳማ ክልል የማልጋ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ በበኩሉ በ2016/2017 ምርት ዘመን በመኸር አዝመራ ከተሸፈነው ማሳ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል።

በማልጋ ወረዳ የሀሩማርሳ ቀበሌ አርሶ አደር አለማየሁ ብርሀኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ በስንዴ ዘር ሸፍነዋል።

ማሳቸው አሲዳማ አፈር በመሆኑ በምርታማነታቸው ላይ ተጽዕኖ ሲያደርስባቸው መቆየቱን አስታውሰው፣ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አሲዳማ አፈርን በማከም በኩታ ገጠም ስንዴ እያላሙ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት ስንዴ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ከለማው መሬት ከ50 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ አቅደው የአረም ሥራን ጨምሮ የሰብል ክትትልና እንክብካቤ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር ደረጀ ከበደ በበኩላቸው እሳቸውን ጨምሮ የቀበሌው አርሶ አደሮች በመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት ከግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

እሳቸውን ጨምሮ 10 አርሶ አደሮች በክላስተር ያለሙት የስንዴ ሰብል በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ለሰብላቸው የአረምና የተባይ ቁጥጥር ሥራ በማከናወናቸው ከዚህ በፊት ከሚያገኙት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችል የግብአት አጠቃቀምና በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የማልጋ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብዙነህ በሺሮ እንዳሉት፣ በወረዳው በ2016/2017 ምርት ዘመን 4ሺህ 700 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ተናግረዋል።

በዘር ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ 1ሺህ 245 ሄክታር የሚሆነው በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሰብሎች በመልካም ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በተለይ ስንዴ ከሄክታር 60 ኩንታል፤ የቢራ ገብስ ደግሞ 39 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ በቅድመ ምርት ግመታ መረጋገጡን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ካለማው የቢራ ገብስ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ከአሰላ ብቅል ፋብሪካ ጋር የገበያ ትስስር መመቻቸቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆንም አውስተዋል። 

"በልማቱ 14 ሺህ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው በልማቱ ውጤታማ እንዲሆኑ ጽህፈት ቤቱ ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው" ብለዋል።

የሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዲሱ ቃሚሶ በመኸር እርሻ አርሶ አደሩን ውጤታማ ለማድረግ  ለግብርና ቴክኖሎጂና ትኩረት በመሰጠቱ የምርት ቁመናው ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

በመኸር እርሻው 24 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ ከዕቅድ በላይ መሳካቱን ጠቁመው፣ በዞኑ በዋናነት እየለሙ ካሉ ሰብሎች መካከል ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላና አተር ይጠቀሳሉ ብለዋል።

በዚህም ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ያሉት አቶ አዲሱ፣ ይህም አርሶ አደሩ በምግብ እራሱን ከመቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችለዋል ብለዋል።


 

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በ2016/2017 ምርት ዘመን በክልሉ በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 140 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

እቅዱን ለማሳካት የሰብል በሽታዎችና ተባይ ቁጥጥር እንዲሁም የእንክብካቤና ክትትል ሥራው በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም