ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው ውጤታማነትና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሳካት በትብብር እንሰራለን- የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው ውጤታማነትና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሳካት በትብብር እንሰራለን- የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦ ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው ውጤታማነትና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሳካት በትብብር እንደሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሁለት ወራት በፊት ወደ ተሟላ ትግበራ መግባቱ ይታወቃል።
የማሻሻያው ዓላማ እና እያስገኛቸው ያሉ ውጤቶች ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም መንግስት በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም የዘርፎችን ምርታማነት በማሳደግ፣ የውጭ ሀዋላ ምንዛሬን ከፍ በማድረግ ወርቅና ቡናን ጨምሮ የወጪ ንግድ ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመርና ሀገራዊ ገቢን በማሳደግ ተስፋ የሚጣልበት ውጤት ማሳየቱን አብራርተዋል።
በማሻሻያ ትግበራ ሂደቱ በዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጠር የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያ፣ ለመሰረታዊ መድሃኒቶች፣ ለዘይትና ሌሎችም ድጎማ የሚሆን ከ328 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አንስተዋል።
ከታክስ ገቢ ባለፉት ሶስት ወራት 180 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጸው፤ ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 71 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ነው ያሉት።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን የመገንባት ግቡን እየመታ መሄዱን አስረድተው፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተደረገው ውይይት ዓላማውን በቅጡ በመገንዘብ ለውጤታማነቱ በጋራ ለመረባረብ ነው ብለዋል።
በውይይቱ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለሰ ዓለሙ፤ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት የአንድን ሀገር ብልፅግና ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀገራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
የኢኮኖሚ እድገት የአንድ ምርጫ ዘመን ስራ አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ የረጅም ዓመታት ተከታታይ ዕድገትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው የሁሉንም ዜጋ ፍላጎት የሚነካ ብሔራዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ገነነ ገረቡ እና የአፋር ህዝብ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ መሀመድ ዳውድ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዓመታትን የወሰደ ድርድር በማድረግ አተገባበሩንና ውጤቱን በተመለከተ የተሟላ ግንዛቤ ይዘናል ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ውጤታማነትና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሳካት በትብብር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የማክር ኢኮኖሚ ማሻሻያው በስኬት እንዲተገበር መንግስት ጉድለቶችን እየተከታተለ ማስተካከል እንዳለበት አንስተው በእነርሱ በኩል የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።