በሶማሌ ክልል ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን እያደራጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን እያደራጁ ነው
ጅግጅጋ፤ ጥቅምት 11/2017 (ኢዜአ)፡- በሶማሌ ክልል ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን እያሰባሰቡ በማደራጀት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለፀ።
በኮሚሽኑ የሶማሌ ክልል የምክክር መድረክ አስተባባሪ አቶ አወል ሁሴን፤ ባለድርሻ አካላቱ በክልሉ ጅግጅጋ ማዕከል ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማደራጀት ሂደትን በቡድን ሆነው እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብና የውይይት መድረክ ዛሬም ቀጥሎ ተወካዮቹ በአምስት ቡድኖች ተለይተው አጀንዳ የማደራጀት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በአጀንዳ የማደራጀት ሂደቱ ከወረዳ ማህበረሰብ የተመረጡ የህብረተሰብ ወኪሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የክልሉ መንግስት ተወካዮች፣ የልዩ ልዩ ማህበራትና ተቋማት እንዲሁም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወኪሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው ብለዋል።
እያንዳንዱ የማህበረሰብ የውይይት ቡድኖች አጀንዳ የማደራጀቱን ስራቸውን አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እያካሄዱ መሆኑንም አቶ አወል አስረድተዋል፡
ባለድርሻ አካላቱ በአጀንዳዎቹ ላይ በጋራ በመምከር የሚያደራጁትን አጀንዳ ለምክክር ኮሚሽኑ እንደሚያስረክቡም ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ. ም የተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በመጪው ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።