ቀጥታ፡

በቀጣዮቹ አሥር ቀናት በአንዳንድ የአገሪቱ አከባቢዎች ዝናብ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦በቀጣዮቹ አሥር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት አካባቢዎች ላይ የዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ። 

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመጪዎቹ አሥር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ለዝናብ አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል ብሏል።

የደቡብ ምዕራብና ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው አኃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩም ጠቁሟል።

በዚህም በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰፊ ቦታዎችን የሸፈነ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም ተገልጿል።

በመካከለኛው፣ በምስራቅና በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ በሚጠናከሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም የአየር ትንበያ መረጃው ያሳያል።

በቀጣዮቹ ቀናት የሚኖረው እርጥበት ቀደም ብለው ለተዘሩና ፍሬ በማፍራት ላይ ለሚገኙ እንዲሁም ዘግይተው ለተዘሩና የእድገት ጊዜያቸውን ላልጨረሱ የመኸር ሰብሎችም ቋሚ ተክሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል። 

እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ለተተከሉ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች የውኃ ፍላጎት መሟላት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

የሚጠበቀው እርጥበት በአዲስ አበባና በከተሞች አካባቢ በከተማ ግብርና ለሚለሙ አትክልቶች በቂ የውኃ አቅርቦት እንዲኖር ከማስቻል አንጻር አዎንታዊ ጎን እንዳለውም ተመላክቷል። 

የሚጠበቀው እርጥበት ለአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች  ለእንሰሳት መኖና  የመጠጥ ውኃ አቅርቦት መሻሻልም ሆነ መጠነኛ የበጋ ወቅት ሰብል ለሚያመርቱ አካባቢዎች የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ተብሏል። 

ውኃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውኃ ለመሰብሰብና ለማከማቸት መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር በመሆኑ ማኅበረሰቡ ለዚህ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበትም ተገልጿል።

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተለይም በደረሱና በመሰብሰብ ላይ በሚገኙ ሰብሎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድርና የሚመለከታቸው አካላት በደረቅ ቀናቶች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ለመሰብሰብ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል።

የሚኖረው የእርጥበት ሁኔታ ለገፀ-ምድር የውኃ ኃብትን ከማጎልበት አንጻር የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ተጠቅሷል።

በቆላማና ውኃ አጠር አካባቢዎች የሚገኘውን እርጥበት የማሰባሰብና በአግባቡ የማከማቸት ተግባራትን ማከናወን የሚያስችል ሥራ መሥራት ያስፈልጋልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም