የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት 'የአፍሪካ አዳራሽ' ሕንፃ ዛሬ ይመረቃል - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት 'የአፍሪካ አዳራሽ' ሕንፃ ዛሬ ይመረቃል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦እድሳት የተደገረለት የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት 'የአፍሪካ አዳራሽ' ሕንፃ ዛሬ ይመረቃል።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አዳራሹን በይፋ ይመርቁታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
እድሳቱ ከተመድ ጠቅላላ ጉባዔ በተገኘ 57 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ መከናወኑ ተገልጿል።
ዕድሳቱ ታሪካዊና ባህላዊ የኪነ ሕንፃ ይዘቶችን ጠብቆ የተከናወነ ሲሆን ዘመናዊ የአፍሪካ ታሪክና ባህል የሚያንፀባርቅና ቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የሚያስችል ቋሚ ዐውደ ርዕይ አለው።
እንደ ኒው ዮርክ እና ጄኔሻ ቢሮዎች ሁሉ ቋሚ ዐውደ ርዕይና አባል ሀገራት ልዩ ሁነቶችን የሚያዘጋጁበት ስፍራ እንደተዘጋጀለትም ተመላክቷል።
'የአፍሪካ አዳራሽ' የሚሰኘው ሕንጻ በአውሮፓዊያኑ ዘመን ቀመር 1963 32 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መክረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሰረቱበት ታሪካዊ አዳራሽ ነው።
የመጀመሪያውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባዔ ለማስተናገድ በቀዳማዊ አፄ ኅይለሥላሴ ትዕዛዝ በፍጥነት የተገነባው ይህ ታሪካዊ አዳራሽ የአፍሪካዊያን ቅርስ ነው።
በተለይም እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፤ በአዳራሹ መስኮቶች ላይ የሳሏቸው መስታዋት ስዕሎች የአፍሪካን የትናንት ጭቆና መጻኢ ተስፋ አመላካች እንደሆኑ ይነገራል።
የአፍሪካ አዳራሽ በኋላ ለአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መስሪያ ቤት በችሮታ ተሰጥቷል።
ይህ ታሪካዊ ሕንፃ ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በኋላ በመንግስታቱ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ጥገና እና ዕድሳት ተደርጎለታል።
ዕድሳቱ የአወቃቅርና ቴክኖሎጂ ማዘመን፣የተሻለና ምቹ አገልግሎት ያለው፣ ቅርሶችን እና ሌሎች ታሪካዊ ይዘቶችን ጠብቆ መከናወኑ የፕሮጀክቱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።