የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ወላይታ ድቻ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።
ቡድኑ በሶስቱ ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ዘጠኝ ጎሎችን አስተናግዷል። ወላይታ ድቻ በሶስት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባካሄዳቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ጎል ተቆጥሮበታል።
በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በአራት ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው የአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአሰልጣኝ አብዱ ቡሊ የሚመራው አዳማ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።
በሁለቱ ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። አዳማ ከተማ በሶስት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በሊጉ ባከናወናቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ሶስት ጎሎችን ሲያገባ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል።
በውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ በአምስት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3 ለ 2 ሲያሸንፍ ስሑል ሕሬ እና ድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
በሌላ በኩል የ2017 የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ዛሬ በሃዋሳ ይጀመራል።
የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ በሃላባ ከተማ እና በባቱ ከተማ መካከል በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ይደረጋል።
ስልጤ ወራቤ ከየካ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 8 ሰዓት እንዲሁም ሻሸመኔ ከተማ ከቦዲቲ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እንደሚሳተፍ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።