ቀጥታ፡

በውሃ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል የፖሊስ ሃይል (ኮስታል ጋርድ) ተደራጅቷል- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሻ ገብረ ሚካኤል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2017(ኢዜአ)፦ ውሃ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል የፖሊስ ሃይል (ኮስታል ጋርድ) መደራጀቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ይህንን የገለጹት በ2016 በወንጀል መከላከል ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፖሊስ አመራሮችና አባላት በተዘጋጀ የዕውቅናና ሽልማት መርኃ ግብር ላይ ነው።

ኮሚሽነር ጀነራሉ በውሃ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የጀልባ ላይ የፖሊስ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ካደጉት አገራት ልምድ በመውሰድና በጥናት ላይ በመመስረት በውሃ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል የፖሊስ ሃይል (ኮስታል ጋርድ) መደራጀቱን ተናግረዋል።

አገልግሎቱን ለማስጀመር ከሰራዊት ምልመላ ጀምሮ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉንና በአጭር ጊዜ ወደ ስራ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ ፍጻሜ መድረሱን ተከትሎ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በአስተማማኝ የፖሊስ ሃይል መጠበቅ የሚያስችል መሆኑንም ኮሚሽነር ጀነራሉ ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በቀጣይ ለሚሰጡ ተልዕኮዎች ብቁና ተወዳዳሪ የፖሊስ አደረጃጀት ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ፈጣን የፖሊስ ጀልባዎችን ለማሰራት ከመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ጋር የውል ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም