ቀጥታ፡

ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘሩ ማንኛውንም ጥቃቶች በብቃት ለመከላከል የፖሊስ ሰራዊቱ በቁርጠኝነት ይሰራል-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2017(ኢዜአ)፦ ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘሩ ማንኛውንም ጥቃቶች በብቃት ለመከላከል የፖሊስ ሰራዊቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

አገርና ህዝብን በጀግንነትና በሰብዓዊነት ላገለገሉ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል መምሪያዎችና አባላት የዕውቅናና ሽልማት  መርኃ ግብር ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በተዘጋጀው በዚህ መርኃ ግብር ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት በመንግስትና ህዝብ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለፈፀሙ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና መምሪያዎች ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ጊዜ የፌዴራል ፖሊስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ የትኛውንም ጥቃቶች መከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘሩ ማንኛውንም ጥቃቶች በብቃት በመከላከል ኢትዮጵያን ለማፅናት የፖሊስ ሰራዊቱ በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የወንጀል መከላከል ሰራዊቱ  ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ያቀፈ ኢትዮጵያዊ ተቋም ነው ብለዋል።

የወንጀል መከላከል ስራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂና የሰው ሃይል መታገዙን ጠቁመው በዚህም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።


 

የፌዴራል ፖሊስ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የትጥቅና የሎጂስቲክ አቅሙን በማሳደግ በተሻለ ብቃት ስራውን እያከናወነ መሆኑንም ነው ያነሱት።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በዚህም በወንጀል መከላከል ዘርፉ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ታግዞ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በ2016 በጀት ዓመት  ኮንትሮባንድን ጨምሮ በልዩ ልዩ የወንጀል መከላከል ስራዎች ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውንም አመልክተዋል።


 

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ባለመቀበል ጥቃት ለመፈፀም ሙከራ ያደረጉ የሽብር ቡድኖችን በላቀ ፖሊሳዊ ተልዕኮ የጀግንነት ገድል ለፈፀሙ አባላትም ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ስራን በቅንጅት በመስራት የተሻለ ውጤት እንዲገኝ እገዛ ላደረጉ የፀጥታና ደህንነት ተቋማትም ዕውቅና ተሰጥቷል።

በዕውቅና መርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና የፌዴራል ፖሊስ አመራርና አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም