የማህበረሰቡ ትብብር ለኮሪደር ልማቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል-አቶ ሙክታር ሳሊህ - ኢዜአ አማርኛ
የማህበረሰቡ ትብብር ለኮሪደር ልማቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል-አቶ ሙክታር ሳሊህ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2017(ኢዜአ)፦ማህበረሰቡ እያደረገው ያለው ትብብር ለኮርደር ልማቱ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገለፁ።
በሀረሪ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ገቢራዊ እየሆነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት አፈፃፀም ውይይት ተደርጎበታል።
አቶ ሙክታር ሳሊህ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት፥በሁሉም ወረዳዎች የኮሪደር ልማቱ የወሰን ማስከበር ስራ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ማህበረሰቡ የኮሪደር ልማቱ የሚነካቸውን ቤቶች በበራሱ ማንሳት መቻሉ ለስራው ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የወሰን ማስከበር ስራ በተሰራባቸው አካባቢዎች ወደ ስራ መግባት እንደሚገባና የወሰን ማስከበር ስራዎች በቀጣዩ ሳምንት እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ መቀመጡም ታውቋል።
የኮሪደር ልማት ስራውን በ 3 ወራት ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን በማስታወስ ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ከሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።