የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የለውጥ ስራዎችና የስራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የስራ ኃላፊዎቹ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ጎብኝተዋል፡፡
ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ሂደት የዜጎችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ በተዘረጉ አሰራሮች፣ በጦር መሳሪያ ምዝገባ፣ በሰው ሀብትና ንብረት አስተዳደር ሲስተሞች ላይ ለጎብኚዎቹ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
የ አይ ሲ ቲ መረጃ ማዕከልና የሬዲዮ ኔትወርክ ኦፕሬሽን ማዕከል በተመሳሳይ የተጎበኘ ሲሆን በኮሚሽኑ የስራ ቦታን ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትም ምልከታ ተደርጎባቸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉብኝቱ ላይ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ወደ ህዝቡ ይበልጥ ለመቅረብና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የጀመራቸው ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው።
ኮሚሽኑ ከህዝቡ እና አመራሩ ጋር ተቀራርቦ በመስራቱ ውጤቶች ተገኝተዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች መዲናዋን የነውጥ ማዕከል ለማድረግ የተሞከሩ ተግባራት በህዝቡና በጸጥታ አካላት ትብብር ውጥናቸው እንዳይሳካ ማድረግ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በመዲናዋ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ ከተማ አስተዳደሩ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመው የከተማ አስተዳደሩ ለፖሊሳዊ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማቅረብ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
ሕዝብን በፍትሃዊነትና በላቀ መልኩ ለማገልገል ኮሚሽኑ የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የከተማዋን ዕድገትና የጸጥታ ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የፖሊስ ኃይል መገንባቱን ተናግረዋል።
ለገባነው ቃል ኪዳን ፤ለተቀበልናቸው የህዝብና የመንግስት አደራ ዛሬም እንደወትሮው የከተማችንን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናችንን ለማረጋገጥ እወዳለሁ ሲሉም ገልጸዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጌቱ ገለጻ በቴክኖሎጂ የታገዘ የወንጀል ምርመራና የትራፊክ አደጋ ቁጥጥር፣ በካሜራ የታገዙ የፖሊስ ጥበቃ አገልግሎቶች ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።
በፖሊስ ጣቢያዎች ግንባታና እድሳት እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን በማስፋፋት በኩል ውጤታማ ስራዎች እንደተከናወኑም ተናግረዋል።