ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች በመለየት እየተካሄደ ባለው አገራዊ የምክክር ሂደት ሁሉም ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል -ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ - ኢዜአ አማርኛ
ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች በመለየት እየተካሄደ ባለው አገራዊ የምክክር ሂደት ሁሉም ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል -ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

ጅግጅጋ፤ ጥቅምት 10/2017(ኢዜአ)፡- ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች በመለየት እየተካሄደ ባለው አገራዊ ምክክር ሂደት ሁሉም ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ነው።
በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ያለመግባባቶችን ለይቶ በምክክር መፍትሄ ለማምጣት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ለሀገራችን የምክክር ሂደት የሚመጥን የአሰራር ስርዓትን ቀርፆ፣ በሀገሪቱ ከ1ሺህ በላይ ወረዳዎችን አካሎ ተሳታፊዎችን በመለየት አሁን ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ላይ ደርሷልም ብለዋል።
ኮሚሽኑ በክልልና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከሀገራችን መዲና አዲስ አበባ ጀምሮ፣ በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በማዕካላዊ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በአፋር ክልል እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላትን በማማከር አጀንዳዎችን መረከቡን ገልፀዋል።
ካላፈው ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሱማሌ ክልል ተመሳሳይ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል ዋና ኮሚሽነሩ።
በክልሉ በጅግጅጋ፣ በጎዴ እና በዶሎ አዶ ማዕከላት ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ከ 1 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ወኪሎችን በማመካከር አጀንዳዎቻቸውን እንዲለዩ ማድረግ መቻሉን በማከል።
በሶስቱም ማዕከላት በነበረው የምክክር መድረክ የማህበረሰብ ተወካዮች የነበራቸው ተሳትፎ እጅግ የሚደነቅ እንደሆነ ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጸው፤ በዚህም በኮሚሽኑ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዛሬ የተጀመረውና የተመረጡ 100 የህብረተሰብ ወኪሎችን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት ተወካዮች፣ የልዩ ልዩ ማህበራትና ተቋማት እንዲሁም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወኪሎች የሚሳተፉበት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚካሄደው በዚሁ የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ከላይ ከተጠቀሱ አምስቱ ባለድርሻ አካላት የተመረጡ ከ1ሺህ 200 በላይ ተወካዮች የሚሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተወካዮቹም በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ወኪሎችን ይመርጣሉ፤ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ አጀንዳዎችንም ለይተው ለኮሚሽኑ የሚያስረክቡ ይሆናል ብለዋል።
የምክክር ሂደቱ እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች የሚለዩበት ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ የማህበረሰብ ወኪሎችና ባለድርሻ አካላት በንቃት በመሳተፍ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች በመለየት በተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ሂደት አሻራችሁን እንድታስቀምጡ አሳስባለሁ ብለዋል።
በጅግጅጋ የሚካሄደው የሶማሌ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የላቀ አጀንዳዎች የሚለዩበት እንደሚሆን ተስፋ ማድረጋቸውን በማከል።