ቀጥታ፡

ከየትኛውም አቅጣጫ ሊከፈቱ የሚችሉ ጥቃቶችን መከላከል የሚችል የአየር ሃይል ተገንብቷል - ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2017 (ኢዜአ)፦ከየትኛውም የሀገራችን አቅጣጫ ሊከፈቱ የሚችሉ ጥቃቶችን መከላከል የሚችልና የሚመጡ አደጋዎችን ለመቀልበስ የሚያስችል የአየር ሃይል ተገንብቷል ሲሉ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

ሌተናል ጀነራል ይልማ፥ አየር ሃይሉን ከነበረበት ውድቀት ለማንሳት በጸጥታ ዘርፉ የተሰሩት ሪፎርሞች ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በሰው ሃይል ግንባታ፣ በትጥቅና በውጊያ መሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡

ለታላቅ ሀገር የሚመጥን ታላቅ የአየር ሀይል የመገንባት ጥረታችንን ዕውን ለማድረግና የነገውን ጠንካራ የአየር ሀይል ለመገንባት ከምልመላ ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ሀገሩንና ሙያውን የሚወድ ከፖለቲካና ሌሎች ተፅዕኖዎች ነፃ የሆነ ፤ ኢትዮጵያን የሚመስል ስብጥር ያለው አመራርና ባለሙያ እየተገነባ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ያሉትን የአየር ሃይል ትጥቆች ከማሻሻል ባለፈ ዓለም የደረሰባቸው ዘመናዊ ትጥቆችን እየታጠቅን እንገኛለን ያሉት ዋና አዛዡ፥ በቅርቡ ከአፍሪካ ጠንካራ አየር ሃይሎች ጎን መሠለፍ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ታሪካዊ ጠላቶቻችን በሀገራችን ላይ የከፈቷቸው የስነልቦና ውጊያዎች መኖራቸውና ለማስፈራራት ከመሞከር ባለፈ የሚያመጡት ውጤት አለመኖሩን ገልፀዋል።

ተላላኪዎችን እየደገፉ ያሉ ጠላቶች ጥቃት ለመክፈት ከሞከሩ እንደአመጣጣቸው ለመመለስ በተሟላ ዝግጁነት ላይ እንገኛለንም ብለዋል።

ሀገራችንንና የአየር ሀይሉን ስም ለማጠልሸት በፅንፈኞች የማህበራዊ ሚዲያዎች የተከፈቱት ዘመቻዎች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በግምት የሚደረግ ምንም ነገር አለመኖሩንና ዘመኑ በፈጠረው ቴክኖሎጂ ተፈላጊ ዒላማን በተፈለገው ቦታና ጊዜ ለይቶ እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል ነው ዋና አዛዡ የገለፁት።

ሆን ተብሎ ሲቪሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ለማስመሰል የሚደረጉ የውሸት የሚዲያ ዘመቻዎች በዘርፉ ዕውቀቱ የሌላቸውን ለማሳሳትና ሽንፈታቸውን ለመደበቅ መሆኑን ገልፀው፥ ሲቪሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከመደረጉም ባለፈ ዒላማዎችን በቁጥር ጭምር መለየት ይቻላልም ነው ያሉት።

በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከሁሉም ሀገራዊ የፀጥታ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝና ለጋራ ተልዕኮ በጋራ የመስራት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልፀዋል።

ለመከላከያ ሠራዊቱ ፤ ለአየር ሀይሉና ለሌሎች የፀጥታ ዘርፎች ውጤታማነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑና የተሻሻለው ፖሊሲ ፣ ስትራቴጂና የሠራዊቱ የግንባታ መመሪያ ተቋማትና አባሉ ከፖለቲካ ወገንተኛነት በመውጣት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉና ሙያዊ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።

ለሀገር መስዋዕትነት ከፍለው ሀገርን ያቆዩና ታሪክ የሰሩ ጀግኖች ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙና ተቋሙን ካገለገሉ ጀግኖች ጋር አብሮ በመስራት ሙያተኞች ተቀጥረው እንዲያገለግሉ ከማድረግ ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች አቅም ያነሳቸውን በተቻለ መጠን እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም