ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የለውጥ ስራዎች በመጎብኘት ላይ ናቸው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2017( ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የለውጥ ስራዎች እና እንቅስቃሴዎች በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡

በጉብኝቱ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ተግባራት በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡

ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ሂደት የዜጎችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችል አሰራር ፣የጦር መሳሪያ ምዝገባና የሰው ሀብትና ንብረት አስተዳደር ሲስተሞች ከሚጎበኙ የለውጥ ስራዎች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡


 

የአይ ሲ ቲ መረጃ ማዕከልና ሬዲዮ ኔትወርክ ኦፕሬሽን ማዕከል እንዲሁ የጉብኝቱ አካል ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሰላምን ለማረጋገጥ የጸጥታ አካላት እና ህብረተሰቡ በትብብር በመስራታቸው በርካታ ውጤት ተገኝቷል፡፡

በቴክኖሎጂ የታገዘ የወንጀል ምርመራና የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል፡፡

የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ የተካሄዱ ሙከራዎችን ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ማክሸፍ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነር ጌቱ ገለጻ፥ ከአዲስ አበባ ዕድገት ጋር የሚጣጣም የፖሊስ ሃይል የተገነባ ሲሆን እንደሁል ጊዜው ግዳጁን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም