የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ በ46ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ በ46ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2017( ኢዜአ):- የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ በ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ፤የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጂራ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ኢትዮጵያ የ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ሆና መመረጧ ይታወሳል።
ጉባዔው የአፍሪካን እግር ኳስ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ የሚያጎለብቱ አዳዲስ ጅምሮች እና አሰራሮች ይተዋወቁበታል ነው የተባለው።
46ኛው የካፍ ጉባኤ ከተለያዩ አባል ማህበራት ተወካዮች መካከል የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ውይይቶች እና የአህጉሩን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።
46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ ከነገ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ።