የስነምግባር መምህሩና የብዝሃ ሕይወት ተንከባካቢው የአባ መፍቀሬ ስብዕ ኪዳነወልድ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈፀመ - ኢዜአ አማርኛ
የስነምግባር መምህሩና የብዝሃ ሕይወት ተንከባካቢው የአባ መፍቀሬ ስብዕ ኪዳነወልድ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈፀመ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፦ የስነምግባር መምህሩና የብዝሃ ሕይወት ተንከባካቢው የአባ መፍቀሬ ስብዕ ኪዳነወልድ የቀብር ስነ-ስርዓት ዛሬ ተፈፅሟል።
አባ መፍቀሬ ሰብዕ ኪዳነ ወልድ በ1921 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ተጉለት ወርቅጉር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አለቃ ወርቅ አገኘሁ አገር ገዳምዬ ሚካኤል፣ ድንቡይ ጊዮርጊስ እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
በልጅነታቸው በገዳምዬ ሚካኤል ለዲቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት ከተማሩ በኋላ ከግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ እጅ ድቁናን ተቀብለው በአካባቢያቸው ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እስከ 14 ዓመታቸው ድረስ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
በተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አድባራት በኃማኖታዊ አስተምህሮ አንድነትን በማስተማር እንዲሁም በብዝኻ ሕይወት እንክብካቤና ጥበቃ ከ70 ዓመት በላይ እንደሰሩም ይነገራል፡፡
በዚህም በደሴና አካባቢው እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የኃይማኖት ተከታዮችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅነትን ያተረፉ ታላቅ አባት ነበሩ።
አባ መፍቀሬ ስብዕ ኪዳነወልድ ከበርካታ ዓመታት አገልግሎታቸው በኃላ በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
የቀብር ስነ-ስርዓታቸውም የደሴና አካባቢው የተለያዩ እምነት ተከታዮች በተገኙበት በሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ እና አቡነ ኢየሱስ ሞአ አንድነት ገዳም ዛሬ መፈጸሙን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።