ቀጥታ፡

የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጀስቲክስ አካዳሚ የሥልጠና መስኩን ለማስፋት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጀስቲክስ አካዳሚ በማሪታይም ዘርፍ የሚሰጠውን የሥልጠና መስክ ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ገለጸ። 

የአካዳሚው ዲን ቺፍ ቴዎድሮስ ሚሊዮን፤ አካዳሚው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የራሱን የባህር ሰራተኞች በራስ አቅም ለማሰልጠን ታስቦ እንደተቋቋመ ጠቁመዋል።

አካዳሚው ላለፉት አስር ዓመታት ለመርከብ ሰራተኞች የማሪታይምና ሎጂስቲክስ እንዲሁም ለባህር ጠላቂዎችና ዋናተኞች የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ጠቁመዋል።


 

በተጨማሪም በሎጂስቲክስ ዘርፉ አጫጭር ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

እስካሁን ባለው በማሪታይምና ሎጂስቲክስ ዘርፍ እንዲሁም ተያያዥ ዘርፎች ከ9 ሺህ 500 በላይ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁንም ገልጸዋል።

ተቋሙ ያሰለጠናቸው ባለሙያዎች በአገር ውስጥና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅቶች ውስጥ ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚከናወነው ንግድ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ በመርከብ መሆኑ ገልፀው ተቋሙ መርከብ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በማሰልጠንና በማብቃት ለዘርፉ እድገት የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቀጣይ ደግሞ ተማሪዎችን በዘርፉ በተለያዩ መስኮች በተለይም በኢንጅነሪንግና በኖቲካል ሳይንስ ኦፊሰሮችን አስተምሮ ለማስመረቅ እንቅስቃሴ መጀመሩ አንስተዋል። 

በሌላ በኩል መርከበኞችን በብዛትና በስፋት ለማሰልጠን እንዲቻል የተለያዩ ትብብሮች ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሰሩ የዘርፉ የሥልጠና ተቋማት ጋር ሥምምነቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

እነዚህ ትብብሮች ከአካዳሚው ሰልጥነው የሚወጡ ተማሪዎችን የሥራ እድል ከመፍጠር አንፃርም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም