ቀጥታ፡

በክልሉ ከ101 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እንደሚለማ ተገለጸ

ቦንጋ፣ ጥምት 9 /2017 (ኢዜአ):- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዘንድሮ የበጋ ወቅት  ከ101 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ  እንደሚለማ  ተገለጸ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የ2017 ምርት ዘመን የበጋ ስንዴና  መደበኛ መስኖ ልማት እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።


 

በዚህ ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ክልሉ ያለውን የግብርና እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት በተቀናጀ መንገድ ይቀጥላል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት አማራጮችን መጠቀም ላይ በተደረገው ትኩረት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ክልሉ ካለው አቅም አኳያ ገና በመሆኑ መሬት ጾም እንዳያድር ሁሉም በትጋት መስራት  እንዳለበት ተናግረዋል።

በመደበኛ መስኖ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተጀመሩ ስራዎችን በተደራጀ ሁኔታ በማስቀጠል ወደ ሁሉም አካባቢዎች ማስፋት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። 

ግብርናን በልዩ ሁኔታ መምራትና አርሶ አደሩን በመደገፍ በበጀት ዓመቱ በሌማት ትሩፋትም ሆነ  በበጋ መስኖ ልማት የተያዙ ዕቅዶችን ማሳካት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብር ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፣ በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወቅት  በመስኖ ከ101 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል።

በዚህም ከ19 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተው፤ ይህን ውጤታማ ለማድረግ የምርጥ ዘርና ግብዓት ስርጭትን ጨምሮ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል ።

በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበጋ መስኖ ልማት በመጠንም ሆነ በምርታማነት እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ዘንድሮም ይህል አጠናክሮ በማስቀጠል የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አንስተዋል።

ለዚህም በየአካባቢው የሚገኙ ተቋማትን በማሳተፍ ጭምር "በጊዜ የለኝም" መንፈስ አሁን ያለውን እርጥበታማ አየር ተጠቅመን እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በክልሉ ያሉትን አማራጮችን ወደ ውጤት በመቀየርና ምርታማነትን በማሳደግ ከቤት ፍጆታ ባለፈ ገበያ ማረጋጋትና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማስፋት ላይ ትኩረት መደረጉንም አቶ ማስረሻ አንስተዋል።

የኮንታ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ማስረሻ አደሮ፣ ባለፉት ዓመታት በዞኑ በበጋ መስኖ ምርታማነት ላይ ትኩረት በመሰጠቱ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። 

በተለይም በዞኑ በበጋ መስኖ ስንዴ የመጣውን ውጤት ለማጠናከር ከ1 ሺህ 250 ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት መታቀዱን ተናግረዋል።

 በዞኑ በመደበኛ መስኖ በአንደኛ ዙር ብቻ 20 ሺህ ሄክታር ለማልማት መታቀዱን  የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ አክሊሉ አማዴ ናቸው። 

በዚህም በእርሻው ዘርፍና በሌማት ትሩፋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በማጠናከር ገበያን ማረጋጋት፣ ሀብት የሚመነጭባቸውና የስራ እድል የሚፈጠርባቸው ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በንቅናቄው መድረክ  የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ እና ከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም