ቀጥታ፡

በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ለ619 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፦ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ለ619 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በዚህም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን ተከትሎ በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡ ተመላክቷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በመንግሥት የተወሰደው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም በርካታ ጉዳዮችን የሚነካ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው ሚና ትልቅ መሆኑን ገልጸው የሥራ እድል ፈጠራ በዋናነት በግሉ ዘርፍ የሚመራ በመሆኑ አምራች ዘርፉን የሚያነቃቃ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ባለፉት ሦስት ወራት 619 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ገልጸው የተፈጠረው የሥራ እድል በሀገር ውስጥ፣ በውጭ እንዲሁም በርቀት ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ያልነበረው የርቀት ሥራ በተወሰኑ ሰዎች በተንጠባጠበ መልኩ እንደነበር አስታውሰው በሩብ ዓመቱ በተደራጀ መንገድ 26 ሺህ ገደማ ዜጎች መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ ዜጎችም እስካሁን 2 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንደተፈጸመላቸው ተናግረዋል።

የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪትን በተመለከተ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ36 በመቶ ጭማሪ እንዳለው አመላክተዋል።

ዜጎች ባሉበት ሆነው በኦንላይን ራሳቸውን አብቅተው ወደ ሥራ የሚገቡበት የኢትዮጵያ የገበያ መረጃ ሥርዓት ትልቅ እድል መፍጠሩንም አንስተዋል።

የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አኳያ 800 ሺህ ገደማ ዜጎች ሥልጠና መውሰዳቸውን ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት።

በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አንዱ የመወዳደሪያ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው የሰለጠነና የበቃ የሰው ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣሪዎችም በቀላል መንገድ የሰለጠነ ባለሙያ የሚመለምሉበት እድል መፈጠሩንም አመላክተዋል።

አፈጻጸሙ ተስፋ ሰጭና እያደገ የመጣ መሆኑን ጠቁመው የተገኘው ውጤትም በእጥፍ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም በ2016 ለሁለት ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ 4 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን አንስተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በአዳዲስ መስኮች ጭምር ዜጎችን ለማሰልጠን የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው የ 5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ የሚጠበቅ መሆኑንም አንስተዋል።

እስካሁንም በዚህ መርኃ ግብር ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ሰልጥነው ሰርቲፊኬት መቀበላቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም