ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ተጋጣሚዎቹን አውቋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ተጋጣሚዎቹን አውቋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2024/25 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ምዕራፍ ውድድር በምድብ ሁለት ተደልድሏል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት በግብጽ ካይሮ አካሂዷል።
የምስራቅ እና መካከለኛው የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) ዞንን ወክሎ በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ 2 ሁለት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ካነሳው የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሳንዳውንስ፣ ከግብጹ ቱታንካሙን እና ከናይጄሪያው ኢዶ ኩዊንስ ክለቦች ጋር ተደልድሏል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ዞን አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ቀጣናውን ወክሎ በሻምፒዮንስ ሊጉ ላይ ይሳተፋል።
በምድብ አንድ የአንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የሞሮኮው አስፋር፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ፣ የሴኔጋሉ አይግልስ ዴላ መዲና እና የደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌስተርን ኬፕ ተደልድለዋል።
የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ዙር ውድድር ከጥቅምት 30 እስከ ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም በሞሮኮ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በስድስት ዞኖች የማጣሪያ ውድድር ተካሄዷል።
የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ክለብ የ400 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኛል። ሁለተኛ የሚወጣው ቡድን የ250 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትለታል።
የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ከእ.አ.አ 2020 አንስቶ እየተካሄደ የሚገኝ አህጉራዊ ውድድር ነው።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሃዋሳ ከተማ፣ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ መቻል፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ሀምበሪቾ፣ ሲዳማ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ልደታ ክፍለ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው።
ባህር ዳር ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደጉ ክለቦች መሆናቸው ይታወቃል።