በዞኑ ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ዲላ ፤ጥቅምት 9/2017 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  ጌዴኦ ዞን ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት  የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

የጌዴኦ ልማት ማህበር ህብረተሰብ በማስተባበር ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በዲላ ከተማ ያስገነባው ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

አዳሪ ትምህርት ቤቱ በልህቀት ማዕከልነት በማገልገል የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ለሚደረገውን ጥረት አጋዠ እንደሚሆን ተመላክቷል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዞኑ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ ቅድመ መደበኛ ደረጃን ጨምሮ የሌሎችንም ትምህርት ቤቶች ግንባታ በመከናወን ላይ ነው።

ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው አዳሪ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።

ትምህርት ቤቱ በልህቀት ማዕከልነት በማገልገል የትምህርት ስብራትን ለመጠገን እንደሚያግዝ አንስተዋል።

በተያዘው ዓመት ህብረተሰቡን በማስተባበር ተጨማሪ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመገንባት ጥረት መጀመራቸውን ገልጸዋል። 


 

የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ያነሱት አስተዳዳሪው፤ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ተወዳዳሪ ዜጋን ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የጌዴኦ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታጠቅ ዶሪ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ከዞኑ አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር በ18 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የአዳሪ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ማመቻቸቱን አስታውቀዋል።

ትምህርት ቤቱ መማሪያ ፣ ማደሪያና ፣ መመገቢያና ሌሎችንም መገልገያዎች ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

አዳሪ ትምህርት ቤቱ 106 ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማር ተግባሩን መጀመሩንም ተናግረዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አለሙ እንደገለጹት፤ በታችኛው የትምህርት እርከን በትኩረት መስራት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ መሠረት ነው።

ዩኒቨርሲቲው አዳሪ ትምህርት ቤቱን በግብዓትና ሙያ በመደገፍ በውጤት የላቁ ተማሪዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የዲላ ዩኒቨርሲቲና የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና  የጌዴኦ ልማት ማህበር የቦርድ አባላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም