ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች - የቀድሞ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት አዛዥ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች - የቀድሞ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት አዛዥ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ዋጋ እንደከፈለችና በቀጣይም ኢትዮጵያ በቀጣናው ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሚናዋን ልታጠናክር እንደሚገባ የቀድሞ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት አዛዥ ገለጹ።
የቀድሞ በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) እና የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ልዑክ (አትሚስ) አዛዥና አሁን ላይ የብሩንዲ መከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ሜጀር ጄኔራል ዲጌያ ዲዮሜዴ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ሚና በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ በተለይም በምስራቅና አፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት በሰላም ማስከበር ከፍተኛ ሚና መጫወቷን አስታውሰዋል።
በተለይም ሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ሥር ኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል በማሰለፍ ለሶማሊያ ሰላም ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባላት ጠንካራ የጸጥታ ኃይል ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በምታደርገው አስተዋጽዖ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለዛሬይቱ ሶማሊያ ጸንቶ መቀጠል የማይተካ ሚና መጫወቷን ጠቅሰው፤ በአህጉሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ ሚናዋን አጠናክራ መቀጠል አለባት ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዘመናዊ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ግንባታ ላይ ያስመዘገበችው ለውጥ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በመከላከያ ዘርፍ በትብብር መሥራት እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ጆክ አንጎክ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ያበረከተችው አስተዋጽዖ እውቅና የሚሰጠውና በየትኛውም የአፍሪካ አገር የማይካድ ሃቅ መሆኑን አንስተዋል።
በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በማምጣት የበለጸገችና ለዜጎቿ ምቹ አህጉርን ለመፍጠር የጸጥታ ተቋማት የተቀናጀ እርምጃ ወሳኝ መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ በአጽንዖት አንስተዋል።