ማህበሩ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ሻሸመኔ ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔና ዶዶላ ለሚገኙ አራት የጤና ተቋማት ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የመድሃኒትና ህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።
ማህበሩ ያበረከተው ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸማኔና ዶዶላ ለሚገኙ አራት የጤና ተቋማት አገልግሎት የሚውል መሆኑን በርክክቡ ወቅት ተገልጿል።
በማህበሩ የምዕራብ አርሲ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ከማል አብደላ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ ጽህፈት ቤቱ የተለያዩ አካላት በማስተባበር ያገኘውን የህክምና ግብዓቶች ድጋፍ አድርጎአል።
በዞኑ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች ያበረከቱ መሆኑን አመልክተው፤ ማህበሩ በዞኑ የተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ የሰብዓዊና ሌሎች ሥራዎች የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ገመዲ በበኩላቸው የተረከቡት መድሃኒቶቹ ወሳኝ የሆኑ እንዲሁም የተለያዩ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶች ናቸው ብለዋል።
በድጋፍ የተገኙ ግብዓቶች በሻሽመኔ ወረዳ ፋጂ ጎሌና ሁርሳ ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም በዶዶላ ወረዳ የሔራሮና ሴሮፍታ ጤና ጣቢያዎች መሰጠቱን አመልክተዋል።
የህክምና ቁሳቁሶቹ ድጋፍ መገኘት በተቋማቱ ያለውን የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት እጥረት በማቃለል የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አንስተው፤ ማህበሩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።