በ12 ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ እየተዘጋጀን ነው- የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በ12 ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ እየተዘጋጀን ነው- የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች
ደሴ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፡- ቀጣይ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተናን ወደ ዩኒቨርሲቲ ማስገባት የሚያስችል ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች ተናገሩ።
የመማር ማስተማር ስራው የተሳካ በማድረግ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት በመስራት ላይ እንደሚገኙ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ብሩክታዊት ሀብቴ፤ ጠንክራ ተምራ በዲጅታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ የማጥናትና የመመራመር ራዕይ እንዳላት ለኢዜአ ተናግራለች።
ለዚህም ቀጣይ ለምትወስደው የ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ እየተዘጋጀች እንደምትገኝ ገልጻለች።
በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ስራው በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሳ፤ ይህን በመጠቀም የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በመትጋት ላይ እንደምትገኝ አመልክታለች።
ሌላው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ወርቁ ሙሉሰው በበኩሉ፤ ትምህርት ቤቱ በውድድር የተሻለ ውጤት እንድናስመዘግብ እድል እየፈጠረልን ነው ብሏል።
የሚሰጠኝን ትምህርት በአግባቡ ተከታትዬ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጀሁ ነው ሲል ገልጿል።
ችግሮችን በመቋቋም በሚፈልጉት ደረጃ ለመድረስ የራስ ጥረት ወሳኝ መሆኑን የቀደሙ ተማሪዎች ባስመዘገቡት ውጤት መረዳቱን የተናገረው ሌላው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ከፍያለው ጓዴ ነው።
በህክምናው ዘርፍ ከአንገት በላይ ቀዶ ህክምና ዶክተር ለመሆን እንደሚፈልግና ይህንን ለማሳካትም ትምህርቱን ጠንክሮ እየጠና መሆኑን አስታውቋል።
በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የባዮሎጂ መምህር ሐጅ ማሞ በበኩላቸው፤ የተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት፣ አቀባበል፣ ተነሳሽነትና ራዕያቸውን ለማሳካት እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከመደበኛው መማር ማስተማር ባለፈ በትርፍ ጊዜያቸው ጭምር እያስጠኗቸውና ያልገባቸውንም እንደሚከልሱላቸው አስረድተዋል።
በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ስራው የተሳካ በማድረግ የማሳለፍ አቅሙን ለማስቀጠል እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ በለጠ ሀይሌ ናቸው።
ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም በትምህርት ቤቱ የተሻለ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ መመቻቸቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተናም ሙሉ ተማሪዎችን በማሳለፍ ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ደግሞ ከተፈተኑት 65 ተማሪዎች 70 በመቶ የሚሆኑት ከ500 በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮም ፈተናውን የሚወስዱ 56 ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ፤ ተሞክሮና ልምዳችንን ለሌሎች ትምህርት ቤቶችም እያካፈልን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ቡድን መሪ አቶ ያሲን አህመድ እንዳሉት፤ በከተማው የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በጥሩ ሁኔታ ቀጥሏል።
በዚህም ቀጣይ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች በየክፍል ደረጃቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ክትትልና ድጋፍም እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተለይ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትን ተሞክሮና ልምድ በማስፋት በሌሎች ትምህርት ቤቶችም የተሻሉ ተማሪዎችን በመለየት ልዩ ክፍል እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፈው ዓመት በመምህር አካለወልድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 76 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በልዩ መምህርና ክፍል በማስተማር 70 ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማድረግ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
ዘንድሮ በሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ልዩ መማሪያ ክፍል እንዲኖር በማድረግ የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ተናገረዋል።
የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል 400 ተማሪዎች ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ከትምህርት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።