ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት ትሰራለች - አምባሳደር ዳባ ደበሌ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት ትሰራለች - አምባሳደር ዳባ ደበሌ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆኗን በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ገለጹ።
አምባሳደር ዳባ በጃፓን የሩሲያ አምባሳደር ኒኮላይ ስታኒስላቮቪች ኖዝድሬቭን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ፣ ዘርፈ ብዙ እና መልካም ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አምባሳደር ዳባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሩሲያን ጨምሮ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በጤና፣ በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢነርጂ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነች ተናግረዋል።
በጃፓን የሩሲያ አምባሳደር ኒኮላይ ስታኒስላቮቪች ኖዝድሬቭ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸው ብሪክስ ይህን ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መልካም እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በቀጣዩ ሳምንት በሩሲያ ካዛን በሚካሄደው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔን አስመልክቶ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
አምባሳደሮቹ የኢትዮጵያ እና ሩሲያ የሁለትዮሽ እንዲሁም በብሪክስ ማዕቀፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።