ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ (UNHCR) አባል መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው ደግሞ በኮሚቴው የአፍሪካን ቡድን በመወክል ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውንም ገልጿል።

ኮሚቴው ዛሬ በጄኔቫ ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማውን አካሄዷል።

የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው የኮሚቴው የአፍሪካን ቡድን በመወክል ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እንዲመረጡ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቋል።


 

አምባሳደር ጸጋአብ ለሶስት ዓመት በኮሚቴው ያገለግላሉ።

ጸጋአብን ጨምሮ የተመረጡት ምክትል ሊቀመንበሮች የአገልግሎት ጊዜያቸውን በሚጨርሱበት የመጨረሻ ዓመት የኮሚቴው ሊቀ መንበርነት ቦታ ይረከባሉ።

አምባሳደሩ በጄኔቫ በጤና ጉዳዮች ላይ የአፍሪካ አምባሳደሮች ቡድን አስተባባሪ እና በተመድ የባለብዙ ወገን መድረኮችን መርተዋል።

ያላቸው ልምድ እና ተሞክሮ በምክትል ሊቀመንበርነት እንደሚረጡ ማስቻሉ ተመላክቷል።

የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በዓመታዊ ግምገማው የኮሚሽኑን ቀጣይ መርሃ ግብሮች እና በጀት ማጽደቁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም