የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች መልስ ዛሬ በአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ወደ ውድድር ይመለሳል።
ፕሪሚየር ሊጉ ከመስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ብሔራዊ ቡድኑ ከጊኒ ጋር በነበረው የማጣሪያ ጨዋታ ተቋርጦ እንደነበር ይታወቃል።
ሊጉ ዛሬ በአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዳግም ሲጀመር ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ሀድያ ሆሳዕና ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ሽንፈት አስተናግዷል።
በሁለቱ ጨዋታዎች 1 ግብ ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዶ በ3 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ በቀሪው አንድ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል።
ሃዋሳ በጨዋታዎቹ 3 ጎሎችን ከመረብ ሲያሳርፍ 4 ግቦች ተቆጥረውበት በ4 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው የአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር መቀሌ 70 እንደርታ ከመቻል ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበት በ4 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ በሊጉ ባካሄዳቸው ሁለት ጨዋታዎች በአንዱ ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፎ በሶስት ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በጨዋታዎቹም 4 ግቦችን ሲያስቆጥር 3 ግቦችን አስተናግዷል።
የሊጉ አራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ስሑል ሽሬ ከሊጉ መሪ ድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ከተማ የአራተኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።
ድሬዳዋ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በሊጉ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።