ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሩብ ዓመቱ የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲመዘገብ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017 (ኢዜአ)፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሩብ ዓመቱ የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉ ተገለጸ።

የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት መካሄድ ጀምሯል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የ8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት የማስመዝገብ ውጥን መያዙን ተናግረዋል፡፡

በ2017 የመጀመሪያው 100 ቀናት ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉም ነው የተገለጸው፡፡

ይህም የተቀመጠው እድገት እንደሚመዘገብ አመላከች ነው ብለዋል።

በተለይ በወጪ ንግድ፣ በመንግስት ገቢ ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግኝት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን አብራርተዋል።

ከወጪ ንግድ አንጻር በተለይ በወርቅ ወጪ ንግድ እጅግ ስኬታማ ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።

ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት ዓመቱን ሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን 4 ቶን ብቻ እንደነበር የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ብቻ 7 ቶን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን ተናግረዋል።

ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ለውጥ ማምጣቱን አመላካች ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቀደም ተብሎ ሰፊ ዝግጅት ተደርጎበት በመተግበሩ ስኬታማ መሆኑን ነው የተናገሩት።


 

በተለይ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የተከናወኑ ስራዎች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በትይዩ ገበያና በባንኮች መካከል ያለው የምንዛሬ ተመን አሁን ላይ እጅግ የተቀራረበ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ያለፉት ሶስት ወራት አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚመዘገብ ያመላከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ የገቢ መሰብሰብ አቅም እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ናቸው።


 

በተያዘው በጀት ዓመት ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እጅግ አበረታች የገቢ አሰባሰብ አፈጻጸም እንዲመዘገብ እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህም በሩብ ዓመቱ 180 ቢሊዮን ብር ገቢ ከታክስ መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ71 ቢሊዮን ብር እድገት እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም