ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የብሪክስ አባል ሀገራት የአፍሪካ መግቢያ በር በሆነችው ኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የብሪክስ አባል ሀገራት የአፍሪካ መግቢያ በር በሆነችው ኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ):- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የብሪክስ አባል ሀገራት የአፍሪካ መግቢያ በር በሆነችው ኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስሯን ማጎልበት እንደምትፈልግም ገልጸዋል።
በሩሲያ ሞስኮ እየተካሄደ የሚገኘው የብሪክስ ቢዝነስ ፎረም ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፎረሙ ተሳታፊዎች በበይነ መረብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዳላት እና በአፍሪካ ሰፊ የገበያ ዕድሎች የያዘች አገር መሆኗን ገልጸዋል።
በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገልግሎቱ በቀዳሚነት ስፍራ ላይ የሚቀመጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ወጣት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅም እንዲሁም ተመጣጣኝ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት አመላክተዋል።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ ምቹ ማድረግን አላማ ያደረገ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ቴሌኮሙኒኬሽን እና ፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተደረጉ ለውጦችንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
መንግስት የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ ላይ በቅርቡ ባደረገው ማሻሻያ ስርዓቱን ገበያው እንዲመራው መደረጉን ገልጸው፤ ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ማሻሻያዎቹ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ እና የባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን መፍጠርን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ገልጸው ይህም ለንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚ ትብብር መልካም አጋጣሚ እና ምቹ እድሎችን የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት በግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ታዳሽ ኃይል የኢንቨስትመንት ዘርፎች የአፍሪካ መግቢያ በር በሆነችው ኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉባቸው ሰፊ እድሎች እንዳሉም ገልጸዋል።
አባል ሀገራቱ ኢትዮጵያ ያሏትን ምቹ እድሎች እና አማራጮች በመጠቀም በተጠቀሱት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የብሪክስ ቢዝነስ ፎረም ዛሬ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ከጥቅምት 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በሩሲያ ካዛን ከተማ እንደሚካሄድ በፎረሙ ላይ ተገልጿል።