ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቢኔውን የ100 ቀን የአፈጻጸም ግምገማ አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቢኔውን የ100 ቀን የአፈጻጸም ግምገማ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚኒስትሮች ምክር ቤትን በመሰብሰብ የካቢኔውን የ100 ቀን የአፈጻጸም ግምገማ ዛሬ ማስጀመራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት አስታወቀ።
ግምገማው የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት እና ቁልፍ የክዋኔ መስፈሪያዎች የቀረቡበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት ገልጿል።
ግምገማው ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዝንባሌዎችን እና ፍኖቶችን በመፈተሽ በኢትዮዽያ ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ ተመልክቷል።
8 ነጥብ 45 በመቶ በተተነበየው የመጪው ዓመት እድገት የለውጡ አበረታች ውጤቶች አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን የሚያሳዩ፣ የጨመረ የመንግሥት ገቢ እና ኢንቨስትመንት ያስገኙ፣ የመንግሥት ዕዳን የቀነሱ፣ በመንግሥት ይዞታ ስር ያሉ ተቋማትን ተወዳዳሪነት የጨመሩ፣ የውጭ ምንዛሪ ያስገኙ፣ የበለጠ ተወዳዳሪነትን የታየበት የፋይናንስ ዘርፍ ያመጡ፣ ምቹ የኢንቬስትመንት ከባቢን የፈጠሩ ብሎም የዘርፍ ምርታማነትን ያሳደጉ መሆናቸው ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በተለይም እንደ ማኑፋክቸሪንግ እና ኮንስትራክሽን ባሉ ዘርፎች የተፋጠነ እንደሚሆን እንደሚጠበቅ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።