የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በቅርቡ ሥራውን ለመጀመር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በቅርቡ ሥራውን ለመጀመር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያን በቅርቡ ለመጀመር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያን ለማጎልበት የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርሟል።
ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን (ዶ/ር)፣ የናይሮቢ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍራንክ ሚዋቲና የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) ፈርመውታል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ከአሁን ቀደም አክስዮን መሸጥ ለሚፈልግ ሰው የሚያገለግል ማዕከላዊ ገበያ አልነበረም።
ይህንንም ተከትሎ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ፈቃድ መስጠት የሚያስችል መመሪያ በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ወደ ትግበራ እንዲገባ መደረጉን ጠቁመዋል።
ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያን ወደ ሥራ ለማስገባት ሕግ ማዘጋጀትና የሰው ኃይል የማደራጀትና የማሰልጠን ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ሥራውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እንዲቻል አስፈላጊ የግብዓት ግዢ በመፈፀም በሙከራ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተለይም አገናኝ አባላት ሆነው የሚያገለገሉ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ደላሎችን በማሰልጠን ሥራውን በቅርቡ ለመጀመር እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጎን ለጎንም ዛሬ የተደረሰው ሥምምነት በዘርፉ ከኬንያ ተሞክሮ ለመውሰድና ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የናይሮቢ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍራንክ ሚዋቲ በበኩላቸው ሥምምነቱ የአገራቱን የውስጥ ገበያ ከማጎልበት ባለፈ ቀጣናዊ ንግዶችን ለማጠናከር የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሥምምነቱ የናይሮቢ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ያለውን ልምድና እውቀት ለኢትዮጵያ በማጋራት የኢትዮጵያን ካፒታል ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ እገዛ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ያለውን እውቀትና ልምድ ለኢትዮጵያ በሚጠቅም መንገድ በማዘጋጀት ተቋማትና ግለሰቦች በካፒታል ገበያው እንዲሳተፉ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ ያለውን የእውቀት ክፍተት በመሙላት በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያው ውስጥ የአገር ውስጥና የውጭ ተሳትፎን ለማሳደግ ሚናውን እንደሚወጣም ተናግረዋል።
የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰነደ መዋለ ንዋይ ገበያ በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መሠረት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትብብር በአክሲዮን ኩባንያነትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንደሚቋቋም ተደንግጓል።