በደሴ ከተማ የወሎ ባህል አምባ አዳራሽና ሌሎችም ተቋማት ታድሰው ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ የወሎ ባህል አምባ አዳራሽና ሌሎችም ተቋማት ታድሰው ለአገልግሎት በቁ

ደሴ ፤ጥቅምት 8/2017 (ኢዜአ)፦ በደሴ ከተማ አስተዳደር ጥንታዊው የወሎ ባህል አምባ አዳራሽን ጨምሮ ከ32 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ የታደሱ የህዝብ ቤተ መጻሕፍትና የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።
በዚሁ ጊዜ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለፁት፤ በተሻለ ደረጃ ታድሰው ዛሬ ለምርቃት የበቁ ፕሮጀክቶች ታሪካዊና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው።
በተለይ በአዲስ መልኩ የተገነባው የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል ወጣቱ አልባሌ ቦታ እንዳይውል ከማድረጉ ባለፈ የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሙሉ ቁሳቁስ የተሟላላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የወሎ ባህል አምባ አዳራሽም ታሪካዊና ታዋቂ አርቲስቶችን ያፈራ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ ባለመታደሱ በእርጅና ምክንያት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በተደረገለት እድሳት በተሟላ መንገድ አገልግሎት መስጠት ይችላል ብለዋል።
የደሴ ቁጥር ሁለት የህዝብ ቤተ መጻህፍትም በአገልግሎት ብዛት ተጎድቶ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ሁሉም በተሻለ ደረጃ ታድሰው በአጭር ጊዜ አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉን ተናግረዋል።
የከተማውን ሰላም በማስጠበቅ ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን በማስተማር ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ክንዱ አዛኔ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቶቹን ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማደስ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህም የወሎን ባህልና ቅርስ ከማስጠበቅ ባለፈ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ''በዚህም የወሎን ባህል ቡድን በማሰልጠን የወሎን ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ እንሰራለን'' ብለዋል።
የወሎ ባህል አምባ የባህል ቡድን አባል አርቲስት ጫኔ ወርቅነህ በሰጠው አስተያየት፤ በርካታ ታዋቂ አርቲስቶችን ያፈራው ወሎ ባህል አምባ በማርጀቱና ባለመታደሱ ለስራ ምቹ ሳይሆን ቆይቷል።
አሁን የመብራት፣ የወንበርና ሌሎች እድሳቶች ተደርገውለት መዘጋጀቱ የኪነ-ጥበብ ስራቸውን በተሻለ ለማከናወን እንደሚያግዛቸው ገልፀዋል።
በምርቃ ስነ-ስርዓቱ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሌሎች አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።