ቀጥታ፡

ከተሞች ተወዳዳሪና ተመራጭ የስራና የመኖሪያ ማዕከላት እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ ነው

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 8/2017 (ኢዜአ)፡-  ከተሞች ያላቸውን ፀጋ በአግባቡ በማልማትና የእርስ በርስ ትስስርን በማጠናከር ተመራጭ የስራና የመኖሪያ ማዕከላት እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱአለም ጤናው ተናገሩ።

የትግራይ ብሔራዊ ክልል 21 ከተሞች ከንቲባዎች እና የዞን አመራር አባላት ዛሬ በድሬዳዋ አስተዳደር ገቢን በማሳደግና በምግብ ራስን ለመቻል በሚያግዛቸው ጉዳዮች ላይ የተሞክሮ ልውውጥ እየተደረገላቸው ይገኛል።

በዚህ የልምድ ልውውጥ ያልተማከለ የፋይናንስ አስተዳደር፣ ማዘጋጃ ቤታዊ የገቢ አሰባሰብ፣ የከተሞች የምግብ ዋስትናና ራስን በመቻል ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጓል።


 

በስልጠናው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱአለም ጤናው እንደተናገሩት፤ የከተሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና ጥያቄዎችን ለማቃለል የገቢ ምንጮችን በአግባቡ መለየትና የተሻለ ገቢ ማስገኘት ይገባል።

በተለይም የከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ከነዋሪዎች ለሚቀርቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ለመመለስ እንደሚያግዝ በመጥቀስ።

በተጨማሪም ከተሞች ያላቸውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፀጋዎችን በአግባቡ በመረዳትና በማልማት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን ማሳካት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የከተሞች መድረክ የኢትዮጵያ ከተሞች ያላቸውን የእርስ በርስ ተሞክሮዎችና ከውጭ አገራት የሚገኙ መሠረታዊ ልምዶች ቀምረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመኖሪያና የስራ ማዕከላት እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ዛሬ በድሬዳዋ መሰጠት የጀመረው ስልጠናና የተሞክሮ ልውውጥ ከተሞች የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ ያግዛል ብለዋል።


 

የትግራይ ብሔራዊ ክልል ጊዜያዊ መንግስት የከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ይህደጎ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ከተሞች የእርስ በርስ ልምድን በመቅሰም የተሻለ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን መሠረታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል ።

በስልጠናው የተሳተፉት 21 የክልሉ ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን በአግባቡ አሟጠው ለመሰብሰብ የተዘጋጀውን መመሪያና በከተሞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመሩትን ተግባራት አጠናክረው ለመቀጠል እንደሚያስችላቸውም በመጠቆም።  

"ስልጠናው በድሬዳዋ እንዲካሄድ የተፈለገው በድሬዳዋ ከተማ በየመስኩ የተሰሩ ሥራዎችና የተገኙትን ተሞክሮዎች ለመቅሰም ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ በአሁኑ ወቅት የአገራችንን ከተሞች በአባልነት አቅፎ ከተሜነትን ለማስፋፋትና የነዋሪዎቹን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የመድረኩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይለማርያም ጌጡ ናቸው።


 

እስከ ነገ በሚቀጥለው ስልጠናና የልምድ ልውውጥ ላይ 21 የክልሉ ከተሞች ከንቲባዎች፣ የከተሞቹ  ስራ አስኪያጆችና  የየዞን አመራር አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም