በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ ሀገራቱ በትብብር መሥራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ ሀገራቱ በትብብር መሥራት አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት እንዲሰፍን እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ ሀገራቱ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በምስራቅ አፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት የከፈለችው መስዋዕትነት በደማቅ ታሪክ የተጻፈ መሆኑን አንስተው ይህን የኢትዮጵያ ሚና ተከትሎ ሀገሪቱን ለማዳከም የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ነው ያመለከቱት።
ኢትዮጵያ አሁንም በቀጣናው የራሷ ሚና ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው የውስጥ ሰላሟንና አንድነቷን ይበልጥ በማጠናከር በቀጣናው ያላትን ሚና አጎልብታ እንድትቀጥል እንደሚያስችላት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት መልካም ስታስብ የኖረች እንደመሆኗ ጎረቤቶቿም ይህን መረዳትና በቀጣናው የትብብር ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የጎረቤት ሰላም የራሴ ሰላም ነው በሚል በተደጋጋሚ በሶማሊያም ሆነ በሌሎች ጎረቤት ሀገራት ላይ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች እንዲፈቱ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር መክፈሏንም ተናግረዋል።
አሸባሪዎች በሶማሊያ በመመሸግ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲያደርሱ እንደነበር አስታውሰው፣ ሽብርተኞችን በመከላከልና በሀገሪቱ ሰላም በማስፈን ረገድ ኢትዮጵያ ያበረከተችው አስተዋጽዖ አይረሴ ነው ብለዋል።
ይሁንና አሁን ያለው የሶማሊያ መንግሥት አመራር የኢትዮጵያን ውለታ በመርሳትና ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር ቀጣናውን ለማተራመስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተገቢ አለመሆኑንና ድርጊቱ በማንም ዘንድ ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት የጎረቤት ሀገራት በመደገፍና በመተባበር ለጋራ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን(ኢጋድ) በቀጣናው ሠላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ በተለይም ሰላምን የሚያደፍረስ እኩይ ተግባር በመከላከል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ፕሮፌሰር ያዕቆብ ጠይቀዋል።