ቀጥታ፡

ምርት ገበያው በሩብ ዓመቱ  5 ነጥብ 3  ቢሊዮን ብር የምርት ግብይት ማከናወኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሩብ ዓመቱ  5 ነጥብ 3  ቢሊዮን ብር የምርት ግብይት ማከናወኑን ገልጿል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በመርኃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት ምርት ገበያው በሩብ ዓመቱ 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር  የሚገመት ምርት አገበያይቷል።

በተለይም በበጀት ዓመቱ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ምሶሶ ተብለው በተለዩ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በዚህም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ምርት ገበያው ለደንበኞቹ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን መስጠቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም ለተለያዩ ምርቶች የሚዛን፣ የመጋዘን እና የግብይት አገልግሎቶች መስጠቱን አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ ምርት ገበያው በሩብ ዓመቱ 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ምርቶችን ማገበያየቱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

ምርት ገበያው በሩብ ዓመቱ ጤፍ፣ ተልባ፣ ዳጉሳ እና የጉሎ ፍሬ እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ቆዳና ሌጦና ጨው፣ ከማዕድን ዘርፍ ሳፋየር፣ ኦፓል እና ኢምራልድን ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርአት ማስገባት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

በዚህም የአዋጭነት ጥናት፣ ኮንትራት ማዘጋጀት፣ ከኢንዱስትሪ ተዋናዮች ጋር ምክክር በማድረግ ለስራው የሚሆን የግብይት ስርአት መዘርጋት የሚያስችል ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከጸደይ ባንክ ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

ምርት ገበያው ለአርሶ አደሮች የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማረጋገጥ ለሚሰራቸው ተግባራት ውጤታማነት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር አብሮ መስራቱ አቅም የሚፈጥርለት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የዛሬውን ስምምነት ጨምሮ ከ 25 የክፍያ ፈጻሚ የፋይናንስ ተቋማት ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት መፈራረሙን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም