የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የብሔራዊ ደህንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው -አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የብሔራዊ ደህንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው -አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የብሔራዊ ደህንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።
"ሉዓላዊነት በምርታማነት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በፓናል ውይይቱ ላይ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የብሔራዊ ደህንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው።
በኢትዮጵያም የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ይህንን እውን ለማድረግ ተጋግዞ መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
ከልመናና ከተረጂነት መውጣት የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን በመገንዘብ የብሔራዊ ደህንነትን የማረጋገጥ ስራን ማፋጠን ይገባል ሲሉም አክለዋል።
የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ስራ ያላሰለሰ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፤በአገሪቱ ለዚህም የሚሆን ምቹ ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል።
በዚህ ላይ እየተሰሩ ያሉ ተቋማዊ ልምምዶችን ማሳደግና ማጠናከር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው የምግብ ሉአላዊነት የብሔራዊ ማንነታችን መገለጫ መሆን አለበት ብለዋል።
በዚህ ላይ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ሳቢና ከብሔራዊ ማንነት ጋር የተሳሰሩ መሆን እንዳለባቸው አመላክተዋል።
እንዲሁም የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማረም እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ተሞክሮዎች እንዲሰፉ እንዲሁም ክስተቶችን ከመንገር ባለፈ አመለካከትን መቀየር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የፓናል ውይይቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የግብርና ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በመተባበር አዘጋጅተውታል።