ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ራይድ ትራንስፖርት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ራይድ ትራንስፖርት በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጋየሁ ገብረ ማርያምና የራይድ ትራንስፖርት የሽያጭና ማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጌታቸው ፈርመውታል።

ሥምምነቱ የራይድ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ደንበኞችን በባንኩ ዲጂታል የክፍያ አማራጮች ክፍያቸውን መፈፀም ለማስቻል፣ራይድ በሚያቀርባቸው የተለያዩ ዲጂታል ፕላትፎርሞች በጋራ ለመሥራት፣ ለኤሌክትሪክ መኪኖች ግዥ የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብና በሌሎች ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጋየሁ ገብረ ማርያም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ሥምምነቱ የራይድ ደንበኞች የባንኩ የሞይባል ባንኪንግ፣ሲቢኢ ብርና በሌሎችም የዲጂታል አማራጮች በመጠቀም ክፍያቸውን ለመፈጸም ያስችላል።

ጎን ለጎንም በሌሎች ዘርፎች ላይ በጋራ ለመሥራት እንደሚያስችል ጠቅሰው፥ሥምምነቱ ከራይድ ትራንስፖርት ጋር ያላቸውን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የራይድ ትራንስፖርት የሽያጭና ማርኬቲንግ ኃላፊ ዘላለም ጌታቸው በበኩላቸው፤የተደረገው ሥምምነት በዲጂታል ሥርዓት ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ለደንበኞች ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ሥምምነቱ በቀጣይም ከባንኩ ጋር ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር እንደሚያችልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም