ቀጥታ፡

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናውን ለማተራመስ የሚደረግ የመሳሪያ ዝውውር ሽብርተኝነትን ይበልጥ የሚያስፋፋ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናውን ለማተራመስ የሚደረግ የመሳሪያ ዝውውር ሽብርተኝነትን ይበልጥ የሚያስፋፋ መሆኑን በመከላከያ ዋር ኮሌጅ የደህንነት፣ የስትራቴጂክ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር አየለ በከሪ ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ፖሊሲ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በጋራ ልማትና የሰላም ሁኔታ ላይ በትብብር መስራትን መሰረት ያደረገ ነው። 

ኢትዮጵያ ከአህጉርም ባለፈ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮ እየፈፀመች ሲሆን በተለይም ደግሞ ለጎረቤት አገር ሶማሊያ ብዙ ዋጋ የከፈለች መሆኑ ይታወቃል።

ለሶማሊያ ህዝብና መንግስት ዘላቂ ሰላም ከፊት በመሰለፍ መስዋእትነት በመክፈል ኢትዮጵያን የሚስተካከል እንደሌለም በርካቶች ምስክርነት ይሰጣሉ። 

ከሶማሊያና ሌሎችም የአካባቢው አገራት ጋር በተለያዩ መስኮች በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በትብብር በመስራትም ትታወቃለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሶማሊያ መንግስት ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ህዝብ የከፈለችውን ሁሉ ዋጋቢስ ለማድረግ ሲጥሩ መስተዋሉ በፍፁም ተገቢነት የሌለው መሆኑ ይነሳል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በመከላከያ ዋር ኮሌጅ የደህንነት፣ የስትራቴጂክ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር አየለ በከሪ፤ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ መስዋእትነት የከፈለችበትና አሁንም የቀጠለችበት መሆኑን አንስተዋል።   

በመሆኑም የኢትዮጵያን ውድ ዋጋ እንዳልነበር ለማድረግ የሚደረግ ጥረት እውነታን የረሳና ክህደት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ያልተገባ ጣልቃ ገብነት በመፍጠር አካባቢውን የግጭትና ትርምስ ማእከል ለማድረግ የሚደረገው ጥረትም ለማንም የማይጠቅም በመሆኑ ሊቆም ይገባል ነው ያሉት።

የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚፃረርና አካባቢውን የስጋት ቀጣና ለማድረግ ከሚጥሩ አካላት ጋር መተባበር እንደሌለበት አንስተዋል። 

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናውን ለማተራመስ የሚደረግ የመሳሪያ ዝውውር ሽብርተኝነትን ይበልጥ የሚያስፋፋ በመሆኑ የጋራ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከ120 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር የማግኘት ሰላማዊ መንገድን በመከተል ጥረቷ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም