ሀገራዊ ህልም ዕውን እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የራሳቸውን ገንቢ ሚና መወጣት አለባቸው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ህልም ዕውን እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የራሳቸውን ገንቢ ሚና መወጣት አለባቸው - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ህልም ዕውን እንዲሆን እንደ ሀገር ባስቀመጥናቸው የጋራ ህልም ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የራሳቸውን ገንቢ ሚና መወጣት አለባቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።
የምክር ቤት አባላት ካለባቸው ሕዝባዊ ኃላፊነት አኳያ የሀገር ህልም እንዲሳካ ከፍተኛ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በሚከታተሏቸውና በሚቆጣጠሯቸው ተቋማት እና በመራጭ ህዝባቸው ውስጥ እንዲሠሩ ያስፈልጋል ብለዋል።
አቶ አደም ፋራህ ይህን የገለጹት በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች አመራሮች እየተሰጠ ባለው ሥልጠና ላይ ነው።
አቶ አደም ለሰልጣኞች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) "የህልም ጉልበት፤ ለእመርታዊ ዕድገት" በሚል መሪ ርዕስ በቀረበው ገለፃ ላይ ከሰልጣኞች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያደርሳትንና ለትውልድ የሚሻገር ህልም ተልማለች፤ ይህም እውን እንዲሆን ምቹ ነባራዊ ሁኔታዎች አሏት ብለዋል።
በመሆኑም የሀገሪቱን ብልጽግና እውን ለማድረግ የጋራ ህልም ሊኖረን እንደሚገባና ይህም እውን እንዲሆን ኃላፊነትን በተገቢው ደረጃ መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል።
ህልምን ህያው ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ትክክለኛ ሐሳብ መሆኑን ገልጸው የመደመር ሐሳብ ኢትዮጵያን ከማሻገር አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጭምር የሚተርፍ እንደሆነም አብራርተዋል።
አያይዘውም ሀገሪቱ ያላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ ከዓላማው ጎን የሚሰለፍ ሕዝብ እንዲሁም የተገነቡ ተቋማት የሀገራችንን ህልም ዕውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች ከሚባሉት ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱ መሆኑንም አስረድተዋል።
ህልም የጋራ መረዳትና ርዕይ ጋር የተገናኘ እንደሆነና በምናቅዳቸው ዕቅዶች፣ ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎችና ከምንሠራቸው ሥራዎች ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ይህን ህልም ዕውን ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ተግዳሮቶች ለመቋቋም የአመራሩ ፅናት፣ የሐሳብና የተግባር አንድነት መኖር፣ ከሕዝብ ጋር በትስስር መሥራት እና የጋራ ህልማችንን በመደመር ዕሳቤ በሕዝብ ዘንድ እንዲሰርጽ መሥራት ወሳኝ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ህልምን አስመልክቶ በቀረበው ገለፃ መሠረት ቻይናን ጨምሮ በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት ለእድገታቸው መሠረት የሆነ ህልም እንዳላቸው ሁሉ ኢትዮጵያም ወደ ብልጽግና የሚያሻግራት የጋራ ህልም አስፈላጊ መሆኑ ተብራርቷል።
ህልም ከትላንት ይልቅ ዛሬ ላይ፣ ከዛሬ ይልቅ ደግሞ ነገ ላይ የሚያተኩር፣ አንዱ ትውልድ የሚጀምረው፣ ቀጣዩ ትውልድ የሚኖረው እንደሆነም ነው የተገለፀው።
የሀገሪቱ ህልም ዕውን የመሆን ትልቅ ተስፋ ከወዲሁ እየታየ መሆኑ፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በለውጡ ውስጥ የገጠሙንን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መምጣቱን በተለይም ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደሆነም ገልጸዋል።
ቡናን ጨምሮ የሀገሪቱ የግብርና ምርቶች በዓለም እና በአፍሪካ የቀዳሚነት ደረጃን እየያዙ መምጣታቸው፣ አለምን ያስደነቀ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች መሠራቱ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ መጠናቀቁ መድረሱ፣ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማት መስፋፋት ማሳያዎች መሆናቸው መገለጹን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።
ህልም ዕውን እንዲሆን በጋራ መሥራት እንደሚገባም አንስተው የአመራር ፅናት፣ ቁርጠኝነት እና በትብብር መስራት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን በመረጃው ተመላክቷል።