ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያን ለማጎልበት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያን ለማጎልበት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት  ተፈረመ።

ስምምነቱን የፈረሙት  የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን(ዶ/ር)፣ የናይሮቢ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍራንክ ሚዋቲና የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈፃሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) ናቸው ።

ስምምነቱ  በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑና ለካፒታል ገበያው ተሳታፊዎች በጋራ ስልጠና መስጠትና ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል። 

የሚኖረው ስምምነት በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የካፒታል ገበያ ለማጎልበት የሚያስችልና የእውቀት ሽግግር፣ አቅም ግንባታና ድንበር ዘለል ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን(ዶ/ር)  እንዳሉት ስምምነቱ ከኬንያ ተሞክሮ ለመውሰድና በዘርፉ ያለውን የእውቀት ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ነው። 

የካፒታል ገበያን ስርዓት ለመገንባት የገበያውን ስነ-ምህዳርን መረዳትን እንደሚጠይቅ አንስተው ስምምነቱ አስፈላጊውን ስነ-ምህዳር ለማወቅ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል። 

የናይሮቢ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍራንክ ሚዋቲ በበኩላቸው ስምምነቱ የአገራቱን የውስጥ ገበያ ከማጎልበት ባለፈ ቀጣናዊ ንግዶችን ለማጠናከር የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም