ሀገራዊ ምርትን ማሳደግና በምግብ እራስን መቻል ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ተኪ የሌለው ምርጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምርትን ማሳደግና በምግብ እራስን መቻል ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ተኪ የሌለው ምርጫ ነው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምርትን ማሳደግና በምግብ እራስን መቻል ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ተኪ የሌለው ምርጫ በመሆኑ ኢትዮጵያ አበክራ እየሰራች ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር ገለጹ።
"ሉአላዊነት በምርታማነት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በፓናል ውይይቱ ላይ እንደገለጹት፥ሀገራዊ ምርትን ማሳደግና በምግብ እራስን መቻል ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ተኪ የሌለው ምርጫ በመሆኑ ኢትዮጵያ አበክራ እየሰራች ነው።
በአገሪቱም የተለያዩ ኢኒሼቲቮች በመቅረጽ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የተሰራው ስራ ከግለሰብ ጀምሮ በምግብ እራስን በመቻል ሂደት ውስጥ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ከራስ ያለፈ ምርት በማምረት ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል አቅም መፍጠር መቻሉን አመላክተዋል።
እየተገኙ ያሉ ለውጦች ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው፥ በምግብ ራስን ለመቻል እየተከናወነ ያለው ስራ ትርጉሙ ብዙ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል በሚደረገው ጥረት ውስጥ በየአካባቢው ያሉ አቅሞችን ወደ ልማት ለማውጣት በትብብር መስራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
መድረኩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የግብርና ሚኒስቴር፣የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በመተባበር ያዘጋጁት ነው።