ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንዳለ በተግባር ማረጋገጥ ተችሏል - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የምግብ ሉአላዊነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንዳለ በተግባር በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

"ሉዓላዊነት በምርታማነት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት የምግብ ሉአላዊነት የኢትዮጵያ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ገለጸዋል።

ባለፉት አመታት ይህንን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንዳለም ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

በቤተሰብ እና በግለሰብ ደረጃ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራዊ ለውጦች መመዝገባቸውንም አንስተዋል።

ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶችንም በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የማስገባት ልምምድን መቀነስ መቻሉን ጠቅስው ትርፍ በማምረት ከራስ አልፎ ለሌሎች ማቅረብ እንደሚቻልም በተግባር ማየት መቻሉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህንን አጠናክሮ ለመቀጠል በቅንጅትና በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው መሰል መድረኮች የላቀ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ መድረኮችን እያዘጋጀ ይገኛል ብለዋል።


 

ከ14 በላይ ትልልቅ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው የፓናል ውይይት መድረኮች በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ተደራሽ ስለመሆናቸውም አስታውስዋል።

የዛሬው መድረክም ከዚያው የቀጠለ መሆኑን ጠቅሰው በወሳኝ ጉዳዮች ላይ የሚካሄዱ የውይይት መድረኮች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመድረኩ የምግብ ሉዓላዊነት ከአገር ሉዓላዊነት ጋር ያለው ትስስር፣ ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ቅነሳ ፖሊሲ አኳያ ያለው መስተጋብር እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና የተመለከቱ መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል። 

በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያሉ ምቹ ሁኔታዎች በውይይቱ በስፋት እንደሚዳሰሱም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም