ለሀገር ይበጃሉ ያልናቸውን አጀንዳዎች አደራጅተን በማቅረብ የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እንወጣለን - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ይበጃሉ ያልናቸውን አጀንዳዎች አደራጅተን በማቅረብ የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እንወጣለን - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች
ጅግጅጋ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር ይበጃሉ የሚሏቸውን አጀንዳዎች አደራጅተው በማቅረብ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡ በሶማሌ ክልል የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በበኩሉ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
ምክር ቤቱ በሶማሌ ክልል ከሚገኙ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ጋር በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ ከተሳተፉት መካከል አብዱማለኪክ ሁሴን(ዶ/ር) እንደተናገሩት በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ የግንዛቤ ማስጨበጫና ሌሎች ስራዎችን በማከናወን የራሳችንን አስተዋጽዎ እያበረከትን እንገኛለን።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በክልሉ በቀጣይ እሁድ በሚያካሂደው የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ ለሀገርና ለህዝብ ይበጃሉ የሚሏቸውን አጀንዳዎች በማቅረብ ለስኬታማነቱ መዘጋጀታቸውን በማንሳት
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለያዘው እቅድ ስኬት እንደ ሴቶች ማህበራትም ሆነ ሲቪል ማህበራት የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እያበረከቱ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ነስራ ዩስፍ ናቸው።
ምክክር ኮሚሽኑ በሚያዘጋጀው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ላይ በመሳተፍ ለሀገር ይጠቅማል፤ ለህዝቡም ይበጃል የሚሏቸውን አጀንዳዎች በማቅረብ አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮ መርዎ አብዲ በበኩላቸው "እንመካከር፤ እንወያይ ማለት እንስማማ እንደማለት ነው" የሚል የሶማሊ ማህበረሰብ አባባል አለ ይላሉ።
በዚህ ምክንያት ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ትክክለኛ ወቅት ላይ የመጣ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፤ እኛ እንደሴቶች ማህበር አጀንዳ የማሰባሰብ ስራው ላይ በሚገባ ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ መስራት የሚያስችል የስምምነት በማከናወን ወደ ስራ መገባቱን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮዽያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ምክር ቤት የፕሮግራምና ልማት አማካሪ ቃለወንጌል ምናለ(ዶ/ር) ናቸው።
ሲቪል ማህበራት ድርጅቶችም ስለ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ተገንዝበው በነቂስ እንዲሳተፉ ከማድረግ አንጻር የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎች ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰበሰቡ እና ድርጅቶቹን የሚወክሉ አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አደራጅተው ለማስረከብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እያካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም እንደ አንድ ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ ጨብጠው በአጀንዳ ማሰባሰቡ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመጪው እሁድ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ከክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እንደሚያከናውን መገለጹ ይታወሳል።