ኢትዮጵያ በፀጥታና ደህንነት ረገድ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራና አስተማማኝ ተቋም ገንብታለች - የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና ወታደራዊ አታሼዎች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በፀጥታና ደህንነት ረገድ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራና አስተማማኝ ተቋም ገንብታለች ሲሉ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና ወታደራዊ አታሼዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የመከላከያ ሚኒስትሮቹና አታሼዎቹ ከጉባዔው ተሳትፎ በተጨማሪ የኢትዮጵያን የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

በዚህም በቢሾፍቱ የሚገኘውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንን ጎብኝተዋል።

እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትንም ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም የኢትዮጵያን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ግንባታ የሚደነቅና በጥሩ ማሳያነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በሳይበር ደህንነት፣ በፋይናንስ ደህንነት፣ በመሰረተ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች የላቀ ቴክኖሎጂና የበቁ ባለሙያዎች እንዳሉ ተገንዝበናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የጤና፣ የግብርና፣ የጸጥታና ደህንነት፣ የሎጅስቲክ፣ የከተማ ልማትና ሌሎች ዘርፎችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለመደገፍ የተጀመረው ጥረት አስደናቂ መሆኑን አንስተዋል።

የዛምቢያ መከላከያ ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያ የጋና ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ፣ የዩጋንዳ የመከላከያ ሚኒስቴር የፖለቲካ ዘርፍ ኮሚሽነር፤ ኢትዮጵያ በጸጥታና ደህንነት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ሌሎችም ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ አሰራሮችን በመዘርጋት በአህጉሪቱ በጥሩ ማሳያነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያና ደህንነት ተቋም ጠንካራ መሰረት ያለው የአፍሪካም ኩራት መሆኑን በጉብኝታችን አረጋግጠናልም ነው ያሉት።


 

የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ፤ ኢትዮጵያ በጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ተሞክሮ ለአፍሪካውያን ማካፈሏን አንስተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የመከላከያ ሚኒስትሮችም የኢትዮጵያን የተቋም ግንባታና ነባራዊ ሁኔታ በማድነቅ በጋራ ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባው ታሪካዊ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ በፓን አፍሪካ ጽንሰ ሃሳብ፤ አፍሪካዊ የሰላምና ጸጥታ ተቋም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ላለፉት ሶሰት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በነበረው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ በአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም