የአየር መንገዱ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበር ለድርጅቱ እድገትና ለሰራተኛው ጥቅም በትጋት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር መንገዱ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበር ለድርጅቱ እድገትና ለሰራተኛው ጥቅም በትጋት ይሰራል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበር ለድርጅቱ እድገትና ለሰራተኛው ጥቅም በትጋት እንደሚሰራ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገለጹ።
ላለፉት አምስት ዓመታት ሁለት ቦታ ተከፍሎ የነበረው የአየር መንገዱ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበር በአንድ ላይ ተዋሕዶ በጋራ መስራት መጀመሩን አስታውቋል።
የተዋሐዱት የኢትዮጵ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበር እና የዛሬ አምስት ዓመት የተመሰረተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበራት ናቸው።
የቀድሞ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ተካልኝ ተርፋሳ፤ በሁለቱ መሰረታዊ ማሕበራት በኩል የነበረው ልዩነትና ገፊ ምክንያት ተፈትቶ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የማሕበራቱ መዋሐድ ለሰራተኛው፣ ለድርጅቱ እድገትና ለሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በትብብር ጠንካራ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበር እንደሚኖርም አረጋግጠዋል።
አዲስ ተመስረቶ የነበረው የሰራተኞች ማሕበር ምክትል ፕሬዚዳንት ማርቆስ እየሱስወርቅ፤ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበራቱ ውሕደት ለድርጅቱ እድገትም ሆነ ለሰራተኛው ተጠቃሚነት ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
አሁን ላይ የተዋሃደው መሰረታዊ የሰራተኞች ማሕበር ፕሬዚዳንት የሆኑት መገርሳ አስፋው፤ ማሕበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ያቀፈ በመሆኑ ውሕደቱ ሁለንተናዊ ጥቅም እንዳለው አስረድተዋል።
የኢትዮጵ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማሕበር በአጠቃላይ ከ12 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ታውቋል።