ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ስኬት አሰባሳቢ የሆነ የጋራ ትርክት መገንባት ይገባል- ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ስኬት አሰባሳቢ የሆነ የጋራ ትርክት መገንባት ይገባል ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት በሰጠው ትኩረት በተለያዩ ዘርፎች ስኬቶች እየተመዘገቡ ቀጥለዋል።

በሂደቱ ስኬቶች እንዳሉ ሆነው እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችም ስላሉ በጋራ እየፈቱ መሄድ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ለኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮች አንደኛው ምክንያት የትርክት መዛባት መሆኑን አንስተዋል።

የተዛቡና ወገንተኝነት የሚንጸባረቅባቸው ነጠላ ትርክቶች የኢትዮጵያን አንድነት፣ አብሮነትና ህብረ-ብሄራዊነት በመሸርሸር ለዋልታ ረገጥ እሳቤና ለግጭት ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ስኬት አሰባሳቢ የሆነ የጋራ ትርክት መገንባት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ማዘመንና መሰልጠን እንዲሁም የፖለቲካ፣ ማህበራዊና የምጣኔ ሃብት ስብራቶችን መጠገን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የትርክት መዛባትን ለማረቅና ለማስተካከል ከልሂቃን ጀምሮ የዜጎችን ተሳትፎ ጭምር በማከል በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ-መንግስት መገንባት እንደሚገባ አንስተዋል። 

ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነት መገኛ በመሆኗ ለሁሉም የሚሆን የጋራ ትርክት በመገንባት ረገድ የሁሉም ትብብርና ተሳትፎ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም