ቀጥታ፡

ሰራተኞች አምራችና ውጤታማ እንዲሆኑ ተቋማት ምቹ ከባቢን መፍጠር እንደሚገባቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2017(ኢዜአ)፦ተቋማት ለሰራተኞች ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር የአዕምሮ ጤናቸው ተጠብቆ ውጤታማና አምራች እንዲሆኑ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ።

የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል "በስራ ቦታችን የአዕምሮ ጤናን ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜው አሁን ነው" በሚል መሪ ሃሳብ የአለም አዕምሮ ጤናን ቀን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂዷል።


 

የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራአስኪያጅ ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬ እንዳሉት ሰራተኞች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በስራ ቦታ የሚያሳልፉ በመሆኑ የስራ ከባቢን ምቹ ማድረግ ለአዕምሮ ጤና አስተዋፅኦ አለው።

ተቋማት የአሰራር ስርአታቸውንና የመስሪያ ቤታቸውን ገፅታ ምቹ በማድረግ ሰራተኞቻቸው የአዕምሮ ጤናቸው ተጠብቆ ውጤታማና አምራች እንዲሆኑ ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ለታካሚዎችና ሰራተኞቹ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር የህንፃ እድሳትና አሰራርን የማዘመን ስራ እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በጤና ሚኒስቴር የተጀመረውን የፅዱ ጤና ተቋም ኢኒሼቲቭን በመቀላቀል የሆስፒታሉን ግቢ የማስዋብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሆስፒታሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሰራተኞቻቸውን ጤንነት ለመከታተል የሚያስችላቸውን የደህንነት ማዕከል ማቋቋም እንዲችሉ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።  

የኢትዮጵያ ሳይኮሎጂ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ሄኖክ ሀይሉ በበኩላቸው ማህበሩ በአዕምሮ ጤና ላይ የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና የሚያሳድጉ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። 


 

የስራ ቦታ ለሰዎች የአዕምሮ ጤንነትና የስነልቦና ደህንነት አስተዋፅኦ እንዳለው አንስተው ምቹ የስራ ከባቢ አለመኖር ለአዕምሮ ጤና መታወክ መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል። 

ላለፉት 30 አመታት የአዕምሮ ህክምና እየተከታተሉ እንደሆነና የአዕምሮ ህመም ህክምና ካገኘ መስራትና ህይወትን መምራት እንደሚቻል የገለፁት ደግሞ የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ እሌኒ ምስጋናው ናቸው።


 

ወይዘሮ እሌኒ ላለፉት 24 አመታት በተለያዩ ቦታዎች እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀው ከ100 በላይ የአዕምሮ ህክምና የሚከታተሉ የማህበሩ አባላት መኖራቸውን ተናግረዋል።

ህክምናቸውን በሚገባ መከታተል መቻላቸውና የቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ስራቸውን በውጤታማነት እንዲያከናውኑ እንደረዳቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም